በተወካዮች ምክር ቤት እና ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሁለት ዋና እንዲሁም ሁለት ምክትል አፈ ጉባዔዎች በድምሩ አራት አፈጉባዔዎች ይገኛሉ፡፡ ምክትሎቹ እንደማንኛውም ምክትል ባለስልጣን ብዙም ትኩረት የሚስብ ስልጣን የላቸውም፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ከምክር ቤቱ ጋር የተያያዙ በርካታ ስልጣንና ተግባራት ቢኖሩትም በንጽጽር ካየነው ከአራቱ አውራ ሆኖ የሚወጣው የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ነው፡፡ ለመሆኑ ስልጣንና ተግባራቱ ምንድናቸው?
ስለ ስልጣኑ ስፋትና ደረጃ ጠቅለል ያለ እይታ እንዲኖረን በተለያዩ ህጎች ለአፈጉባዔው የተሰጡ ስልጣንና ተግባራት በአጭሩ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል፡፡
ከዚያ በፊት ግን ስለ ስልጣኑ ደረጃ እና ስለ ህገ መንግስታዊ ሚናው ጥቂት ነጥቦች ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ አፈጉባዔ ከፍተኛ ከሚባሉ የመንግስት ባለስልጣናት ረድፍ ይመደባል፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ፕሬዚዳንቱ ከሞተ፤ ስልጣን ከለቀቀ ወይም በማናቸውም ምክንያት በፕሬዚዳንትነት መቀጠል ካልቻለ በስልጣን ሽግግሩ (presidential line of succession) ከምክትል ፕሬዚዳንቱ ቀጥሎ የሚገኘው አፈጉባዔው ነው፡፡
የዲሞክራሲ ባህል ባልዳበረበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር አፈጉባዔው ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ በፓርላማ ውስጥ ስልጣን ከጨበጠው ፓርቲ በተጨማሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካሉ ይህ ሚናው በተጨባጭ ይታያል፡፡ የህዝብ ተወካዮች የመረጣቸውን ህዝብ ጥቅምና መብት የሚያስጠብቁት ፓርላማ ውስጥ በመናገር፤ በመወያየትና በመከራከር ብሎም ለቆሙለት ዓላማ ድምጻቸውን በመስጠት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የአፈጉባዔው ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
በአፈጉባዔነት ለማገልገል የተለየ ክህሎትና ሙያ ወይም ችሎታ አይጠይቅም፡፡ ጥሩ የሚባል አፈጉባዔ ትልቁ መመዘኛው ገለልተኛ መሆን መቻሉ ላይ ነው፡፡ ለቦታው ታጭቶ ከተመረጠ በኋላ ዕውቀቱንና ጉልበቱን ማዋል ያለበት የወከለውን ፓርቲ ጥቅም በማስጠበቅ ሳይሆን ሁሉንም በህዝብ የተመረጡ ተወካዮች በማገልገል መሆን አለበት፡፡ በእንግሊዝ አፈጉባዔው ከተሾመበት ቀን ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነቱን ማቋረጥ አለበት፡፡ ይህን ነጥብ አስመልክቶ በፓርላማው ድረ-ገፅ ላይ የሰፈረውን የሚከተለውን ጠቃሚ መረጃ ማየቱ ከአገራችን ሁኔታ ጋር ያለውን ልዩነት ለማነጻጸር ያህል ይረዳል፡፡
Speakers must be politically impartial. Therefore, on election the new Speaker must resign from their political party and remain separate from political issues even in retirement. However, the Speaker will deal with their constituents’ problems like a normal MP.
በአገራችን ይህ መሰረታዊ ነጥብ ብዙም ትኩረት አላገኘም፡፡ በዚህ የተነሳ አፈ ጉባዔው ስብሰባ በሚመራበት ወቅት ገለልተኛ፤ ፍትሀዊና ሚዛናዊ የሆነ መርህን መከተል እንዳለበት ከሚያሳስቡ ጥቂት ድንጋጌዎች[1] በስተቀር ገለልተኝነቱን የሚያረጋግጡ ህገ መንግስታዊ መርሆዎች ሆነ የህግ ማዕቀፎች የሉም፡፡
መብት፤ ጥቅምና ክብር
ከመብት ጥቅምና ክብር አንጻር የተወካዮች ም/ቤት አፈጉባዔ የሚኒስትር ማዕረግ ባላቸው ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ተርታ ይሰለፋል፡፡ ከስልጣናቱና መብቶቹ መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
- ከአፈ ጉባዔነቱ ሲነሳ ለከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችን (ሚኒስትር፤ ሚኒስትር ዴኤታ እና ምክትል ሚኒስትር) መብትና ጥቅም ያገኛል፡፡[2] በምክር ቤት አባልነቱ ከሚያገኘው የመቋቋሚያ አበል፤ የስንብት ክፍያ እንዲሁም የመጓጓዣና የጓጓ ማንሻ አበል በተጨማሪ ሌሎች አባላት የማያገኙትን የመኖሪያ ቤት አበል፤ የተሸከርካሪ አበል፤ የሕክምና አገልግሎት፤ የግል ደህንነት ጥበቃ አገልግሎት እና በአፈ ጉባዔነት ሲሾም የመቋቋሚያ የሁለት ወር ደመወዝ ይሰጠዋል፡፡
- የሪፐብሊኩን ሰንደቅ ዓላማ በተሸከርካሪ ላይ በመስቀል መጠቀም ይችላል፡፡ ይህ ልዩ መብት የተሰጣቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔና ምክትል አፈ ጉባዔ፤ የፌደራል መንግስቱ ሚኒስትሮች፤ የሀገሪቱ የጦር ሀይሎች ኤታማጆር ሹም፤ የፌደራል ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶችና የክልል መንግስታት ፕሬዚዳንቶች[3] ናቸው፡፡
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በስራ ላይ በማይሆንበት ጊዜ ብሔራዊ የሃዘን ቀንና ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ የሚውለበለብባቸውን ሁኔታዎች ይወሰናል፡፡[4]
ጠቅላላ ስልጣናት
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባዔ ስልጣንና ተግባራት በአንቀጽ 66 ላይ በግልጽ ያስቀመጠ ቢሆንም የተወካዮች ም/ቤት አፈጉባዔውን ስልጣንና ተግባር በዝምታ አልፎታል፡፡ በአንቀጽ 58/4/ ምክር ቤቱ ዕረፍት ላይ በሚሆንበት ጊዜ ስብሰባ እንደሚጠራ ከማመልከት በስተቀር ስለ ስልጣኑ የሚናገር ድንጋጌ የለም፡፡ በአንቀጽ 66 የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባዔው የሚከተሉት ስልጣንና ተገባረት አሉት፡፡
- የምክር ቤቱን ስብሰባዎች ይመራል፡፡
- ምክር ቤቱን በመወከል ጠቅላላ የአስተዳደደር ስራዎች ይሰራል፡፡
- ምክር ቤቱ በአባሎቹ የወሰነውን የዲሲፕሊን እርምጃ ያስፈጽማል፡፡
በህገ መንግስቱ በዝምታ ቢታለፍም የተወካዮች ም/ቤት አፈጉባዔ ከላይ የተዘረዘሩትን ጨምሮ ሌሎች ስልጣንና ተግባራት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራርና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ ቁ. 6/2008 ዓ.ም. አንቀጽ 9 ላይ ተሰጥቶታል፡፡ ከእነዚሀ መካከል በዋነኛነት የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
- ምክር ቤቱን በበላይነት ይመራል፡፡ ያስተዳድራል፡፡
- የምክር ቤቱን ስብሰባዎች ይመራል፡፡ ስነ-ስርዓት ያስከብራል፡፡ ልዩና አስቸኳይ ስብሰባዎች ይጠራል፡፡
- በስብሰባ ወቅት ለሚነሱ የትርጉም ጥያቄዎች ውሳኔ ይሰጣል ወይም ለሚመለከተው አካል ይመራል፡፡
- የኮሚቴዎችን ሊቃነመናብርት፤ ምክትል ሊቃነመናብርት እና አባላት እንዲሁም ምክር ቤቱ በሕግ መሰረት በሚወከልባቸው አካላት ውስጥ የሚወከሉ አባላትን ያስመርጣል፡፡ እንዲወከሉ ያደርጋል፡፡
- የቋሚ ኮሚቴዎችን ስራ ያስተባብራል፡፡
- ምክር ቤቱን በመወከል ግንኙነት ያደርጋል፡፡
ከላይ በጥቅል አነጋገር የተጠቀሱት ስልጣናት በም/ቤቱ ደንብና ደንቡን ተከትሎ በወጡ ወደ 29 የሚጠጉ መመሪያዎች እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ህጎች አንድ በአንድ ተዘርዝረዋል፡፡
የምክር ቤቱን ስብሰባ የመምራት ስልጣን
አፈ ጉባዔ በምክር ቤቱ በሚከናኑ ማናቸውም ተግባራት ላይ ሁሉ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ እጁ አለበት፡፡ በጥያቄ[5] እና ሞሽን[6] አቀራረብ፤ በአጀንዳ አቀራረጽ፤[7] የውይይት ጊዜ አመዳደብ እና የተናጋሪ አመራረጥ፤[8] የስነ-ስርዓት ጥያቄ አቀራረብ፤[9] ድምጽ አሰጣጥ[10] እና ሌሎችም ጉዳዮች በአፈጉባዔው ተጽዕኖ ስር ናቸው፡፡
ለምሳሌ ስብሰባ በመምራት ስልጣኑ በሚከተሉት ምክንያቶች ስብሰባ ሊያቋርጥ ይችላል፡፡[11]
- የስነ ስርዓት ወይም የስነ ምግባር ጉድለት የዕለቱን ስብሰባ ሂደት በጎላ መልኩ የሚያውክ መሆኑን ከተገነዘበ
- በስነ ስርዓት ወይም በስነ ምግባር ጉድለት ምክንያት የፀጥታ መደፍረስ የተፈጠረ ከሆነ ወይም ሊፈጠር ይችላል ብሎ ካመነ/ከገመተ
- የስነ ስርዓት ወይም የስነ ምግባር ጉድለቱ በአባላት መካከል ጠብ ሊያስነሳ የሚችል መሆኑን ከተገነዘበ
- የመናገር ዕድል ሳይሰጠው እንደተሰጠው በመቁጠር ንግግር የጀመረ አባል በሚኖርበት ጊዜ አፈጉባዔው ንግግሩን አስቁሞ ለተፈቀደለት አባል ይሰጣል፡፡[12]
- በአጀንዳነት የቀረበ ጉዳይ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ በቂ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ወይም አፈጉባዔው በቂ ውይይት ተደርጓል ብሎ ሲያምን ድምጽ እንዲሰጥበት ያደርጋል፡፡[13]
የምክር ቤቱን አሰራር የሚመለከት ሞሽን ማለትም ምክር ቤቱ የሚወያይበትን አጀንዳ ወይም ሂደት በተመለከተ የሚቀርብ የስነ ስርዓት ጥያቄ ውሳኔ የሚያገኘው በአፈጉባዔው ነው፡፡[14] የስነ ስርዓት ጥያቄን በሚመለከት ምክር ቤቱ በ2000 ዓ.ም. ባወጣው መመሪያ[15] ላይ በዝርዝር የተቀመጠ ሲሆን በመመሪያው መሰረት አፈጉባዔው የሚከተሉት ስልጣናት አሉት፡፡
- ለጥያቄ አቅራቢው ዕድል የመስጠት
- ጥያቄው የስነ ስርዓት ጥያቄ መሆን ወይም አለመሆኑን የመወሰን
- አለአግባብ የቀረበን የስነ ስርዓት ጥያቄን የማስቆም
አፈጉባዔው በስነ ስርዓት ጥያቄ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ሲሆን ውሳኔ በሰጠበት ጥያቄ ላይ ድጋሚ ጥያቄ ሊቀርብ አይችልም፡፡ በስነ ስርዓት ጥያቄ ላይ ሆነ ሌሎች በእርሱ ስልጣን ስር በሚወድቁ ጉዳዮች ላይ አፈጉባዔው ውሳኔ በሚሰጥበት ወቅት፤
- በማንኛውም አባል ተቃውሞ፤ ጥያቄ፤ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ትችት ሊቀርብበት አይችልም፡፡
- ማንኛውም አባል ትርጉም ሊሰጠው ወይም እንዲተረጎም ሊጠይቅ አይችልም፡፡
- ምክንያት ሊቀርብበት ወይም አፈጉባዔው ምክንያት እንዲያቀርብበት ሊጠየቅ አይችልም፡፡
- በሚመለከተው ማንኛውም ሰው ተግባራዊ መደረግ አለበት፡፡
በእርግጥ ማንኛውም አባል መሰረታዊ ሞሽን ካቀረበ ከላይ በተዘረዘሩት ነጥቦች ላይ ምክር ቤቱ ሊወያየበት ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የሞሽን አቀራረብ ስርዓቱ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የአፈጉባዔውን ይሁንታ ማግኘት አለበት፡፡ ማንኛውም ሞሽን የሚቀርበው በምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ ወይም በአፈጉባዔው ሲፈቀድ ነው፡፡[16] አፈጉባዔው የዚህ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደመሆኑ ከላይ በተዘረዘሩት ነጥቦች ላይ እርሱ ካልፈቀደ በስተቀር በምክር ቤቱ የሚታይበት አጋጣሚ የለም፡፡
ይግባኝ ሰሚ
- ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመምሪያ ኃላፊዎች ላይ የሚተላለፍ አስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ይግባኝ ይሰማል፡፡[17]
- በምክር ቤቱ አባላት ላይ የመብት መጣስ ተግባር ሲፈጸም ጉዳዩ አብዛኛውን አባል የሚመለከት ካልሆነ በስተቀር አቤቱታ የሚቀርበው ለህግ፤ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው፡፡ ኮሚቴው አቤቱታውን አጣርቶ ለአፈጉባዔው የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል፡፡ አፈጉባዔው ደግሞ የራሱን ውሳኔ ይሰጣል፡፡[18]
ዕጩ አቅራቢና ሿሚ
- የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነርና ምክትል ኮሚሽነር ዕጩዎችን እንዲሁም ዋና ዕንባ ጠባቂ፤ ምክትክ ዋና ዕንባ ጠባቂና ሌሎች ዕንባ ጠባቂዎችን የሚመለምለው የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነው[19]፡፡
- የፌደራል ዋና ኦዲተር እና ምክትል ዋና ኦዲተሮች ቦታ በተመሳሳይ ጊዜ ክፍት የሆነ እንደሆነ የኦዲት ዳይሬክተሮችን ለሶስት ወራት ጊዜ መድቦ ሊያሰራ ይችላል፡፡[20]
- ከመንግስት ዋና ተጠሪና ከዋና ተቃዋሚ ፓርቲ ዋና ተጠሪ ጋር በመመካከር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ፀሀፊ ይመድባል፡፡ ምክትል ፀሀፊውንና ሌሎች የመምሪያ ሀላፊዎችን ደግሞ በዋና ፀሀፊው አቅራቢነት ብቻውን (መመካከር ሳያስፈልገው) ይሾማል፡፡[21] ዋናው፤ ምክትሉና የመምሪያ ሀላፊዎች በፌደራል የመንግስት ሰራተኞች ህግ ተፈጻሚ አይሆንባቸውም፡፡ የስራ ሁኔታቸው የሚወሰነው አፈ ጉባዔው ብቻውን በሚያወጣው መመሪያ ነው፡፡[22]
አባል እና ሰብሳቢ
- የሀገር አቀፍ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ምክር ቤት አባል ነው፡፡[23]
- በምክር ቤቱ የኮሚቴዎች አደረጃት መሰረት ስድስት ዓይነት ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል፡፡ እነዚህም፤ የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ፤ አስተባባሪ ኮሚቴ፤ ልዩ ኮሚቴ፤ ቋሚ ኮሚቴ፤ ንዑስ ኮሚቴ፤ ጊዜያዊ ኮሚቴ ናቸው፡፡ በልዩ ኮሚቴነት የተዋቀረው የመከላከያና የብሔራዊ መረጃ ደህንነት ጉዳዮች ልዩ ኮሚቴ ብቻ ሲሆን በቋሚ ኮሚቴ ስር 18 ኮሚቴዎች ይገኛሉ፡፡ ከስድስቱ የኮሚቴ ዓይነቶች መካከል ጠንካራ የሚባሉት የሶስቱ ማለትም የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ፤ የመከላከያና የብሔራዊ መረጃ ደህንነት ጉዳዮች ልዩ ኮሚቴ እና የአስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነው፡፡[24]
- በምክር ቤቱ ውስጥ ሴቶችን የሚመለከቱ ሁለት ኮሚቴዎች ይገኛሉ፡፡ አንደኛው የሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሴቶች ኮከስ ተብሎ የሚጠራ ቡድን ነው፡፡ ይህ አካል ዋነኛ ትኩረቱ በሴት አባላት ልምድ ልውውጥ እንዲሁም የሴቶችን መብትና ተጠቃሚነት የሚመለከቱ አጀንዳዎች ምክክር ማካሄድ ላይ ነው፡፡ ይህ ኮከስ ተጠሪነቱ ለአፈ ጉባዔው ነው፡፡
የዲሲፕሊን እርምጃ
የንግግር ስነ ስርዓት ወይም ስነ ምግባር የጣሰ አባል ንግግር ያስቆማል፡፡ አባሉን በስም ጠቅሶ የእርምት ማሳሰቢያ ይሰጣል፡፡ ማሳሰቢያውን የማያከብር ከሆነ ወይም ከስነ ስርዓት ወይም ከስነ ምግባር ውጭ የሆነ ባህሪ አሳይቷል ብሎ ካመነ ከስብሰባ እንዲወጣ ሊያዝ ይችላል፡፡ ከዚያም አልፎ እንደሁኔታው እስከ ሁለት ተከታታይ የስብሰባ ቀናት በአፈጉባዔው ሊታገድ ይችላል፡፡[25]
ሕግ ማውጣትና መተርጎም
- በምክር ቤቱ የፀደቀ ህግ ፕሬዚዳንቱ በ15 ቀናት ውስጥ ካልፈረመበት በአፈ ጉባዔው ስምና ፊርማ ወጥቶ ስራ ላይ ይውላል፡፡ ህጉ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከመውጣቱ በፊት የቴክኒክ እርምት ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ብቻውን እርምት ያደርጋል፡፡[26]
- አዋጅ ቁ. 906/2007 ‘ን’ (የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤትን እንደገና ለማቋቋም የወጣው አዋጅ) ለማስፈጸም ብቻውን መመሪያ የማውጣት ስልጣን ተሰጥቶታል፡:[27]
- ምክር ቤቱ የሚያወጣው የአሠራርና የስነ ምግባር ደንብ ለማስፈጸም የሚረዱ መመሪያዎችን ለማውጣት ስልጣን የተሰጠው ለምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ ሲሆን አፈጉባዔው የዚህ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነው፡፡
- በህግ ተርጓሚነት ሚናው በስብሰባ ወቅት የደንብ ቁ. 6/2008 ይዘትን አስመልክቶ የትርጉም ጥያቄ ከተነሳ ደንቡን የመተርጎም ስልጣን አለው፡፡
በጀት
በረቂቅ በጀት የመገምገምና የውሳኔ ሀሳብ የማቅረብ ሂደት ላይ የአፈ ጉባዔው ሚና ጎልቶ ይወጣል፡፡ አስራ ስምንቱም ቋሚ ኮሚቴዎች በተቋቋሙበት ዘርፍ ያከናወኑትን ተግባር በተመለከተ ሪፖርት ወይም የውሳኔ ሀሳብ ወይም ውሳኔ የሚያቀርቡት በዋናነኛነት ለአፈ ጉባዔው ወይም በቀጥታ ለምክር ቤቱ ሲሆን የሁሉም ተጠሪነት ለምክር ቤቱ ነው፡፡ አፈጉባዔው ከቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን ሪፖርት፤ የውሳኔ ሀሳብ ሆነ ውሳኔ እንደገና የመከለስና የማስተካከል ስልጣን የለውም፡፡ ሆኖም ረቂቅ በጀትን በተመለከተ አሰራሩ የተለየ አካሄድ ይከተላል፡፡
የበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ በተለያየ ሂደት ያለፈውን የመጨረሻውን ረቂቅ በጀት ከመረመረ በኋላ አስተያየቱን ወይም የውሳኔ ሀሳቡን በቀጥታ ለምክር ቤቱ አያቀርብም፡፡ ከዚያ ይልቅ አስተያየቱን በአፈ ጉባዔው በኩል ለምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ ይልካል፡፡ ኮሚቴው የተላከለትን አስተያየት እንደገና በመመርመር የራሱን የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤት ያቀርባል፡፡[28] የዚህ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ ደግሞ አፈጉባዔው ነው፡፡
[1] የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምክር ቤቱ የክርክርና የውይይት ስነ ስርዓት መመሪያ ቁ. 16/2001 ዓ.ም. አንቀጽ 25/2/ ሀ
[2]አዋጅ ቁ. 653/2001 ከሀላፊነት የተነሱ የሀገርና የመንግስት መሪዎች፤ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች፤ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች መብቶችና ጥቅሞች አዋጅ በተጨማሪም አዋጅ ቁ. 934/2008 ከሀላፊነት የተነሱ የሀገርና የመንግስት መሪዎች፤ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች፤ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች የሚያገኟቸውን መብቶችና ጥቅሞች መወሰኛ /ማሻሻያ/ አዋጅ ይመለከቷል፡፡
[3] አዋጅ ቁ. 654/2001 የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ አንቀጽ 21/3/
[4] አዋጅ ቁ. 863/2006 የሰንደቅ ዓላማ /ማሻሻያ/ አዋጅ አንቀጽ 2/2/
[5] የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ ጥያቄ አቀራረብ የወጣ መመሪያ ቁ. 2/2000 ዓ.ም.
[6] የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ ሞሽን አቀራረብ የወጣ መመሪያ ቁ. 3/2000 ዓ.ም. እንዲሁም ስለ ማሻሻያ ሞሽን አቀራረብ የወጣ መመሪያ ቁ. 4/2000 ዓ.ም.
[7] የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአጀንዳ አቀራረፅ የሚመራበትን አሠራር ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁ. 5/2000 ዓ.ም. እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዕለታዊ አጀንዳ ያልተቀረፀ ጉዳይ በምክር ቤቱ እንዲታይ ሞሽን ስለማቅረብ የወጣ መመሪያ ቁ. 8/2000 ዓ.ም.
[8] የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውይይት ጊዜ አመዳደብ እና የተናጋሪ አመራረጥ የሚመራበትን አሠራር ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁ. 6/2000 ዓ.ም.
[9] የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስነ ስርዓት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስነ-ስርዓት ጥያቄ አቀራረብን ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁጥር 7/2000
[10] የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የድምጽ አሰጣጥ መመሪያ ቁ. 9/2000 ዓ.ም.
[11] መመሪያ ቁ. 16/2001 ዓ.ም. አንቀጽ 47/1/
[12] ደንብ ቁ. 6/2008 አንቀጽ 29/4/)
[13] መመሪያ ቁ. 9/2000 ዓ.ም. አንቀጽ 12/1/
[14] ደንብ ቁ. 6/2008 አንቀጽ 44/1/
[15] መመሪያ ቁጥር 7/2000 ዓ.ም. አንቀጽ 10
[16] ደንብ ቁ. 6/2008 አንቀጽ 39/2/
[17] አዋጅ ቁ. 210/1992 እና አዋጅ ቁ. 211/1992 የሁለቱም አንቀጽ 32
[18] ደንብ ቁ. 6/2008 አንቀጽ 142/1/ /3/ እና /4/
[19] አዋጅ ቁ. 210/1992 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ እና አዋጅ ቁ. 211/1992 የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅ የሁለቱም አንቀጽ 11
[20] አዋጅ ቁ. 982/2008 የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ አንቀጽ 12/3/
[21] አዋጅ ቁ. 906/2007 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤትን እንደገና ለማቋቋም የወጣ አዋጅ አንቀጽ 6/1/ ሀ እና ለ
[22] አዋጅ ቁ. 906/2007 አንቀጽ 6/3/
[23] አዋጅ ቁ. 276/1994 ሀገር አቀፍ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ምክር ቤት እና የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 4/3/
[24] ደንብ ቁ. 6/2008 ዓ.ም. አንቀጽ 152፤ 155 እና 160
[25] የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የስነ ምግባር መመሪያ ቁ. 24/2001 ዓ.ም. አንቀጽ 21/1-5/
[26] ደንብ ቁ. 6/2008 ዓ.ም. አንቀጽ 58
[27] አዋጅ ቁ. 906/2007 አንቀጽ 11
[28] የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀት አፀዳደቅ ሂደትን ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁጥር 10/2000 ዓ.ም. አንቀጽ 10/1/ እንዲሁም የምክር ቤቱን በጀት በተመለከተ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራርና የአባላት የሥነ-ምግባር ደንብ ቁ.6/2008 ዓ.ም. አንቀጽ 214
Filed under:
Articles