Quantcast
Channel: Articles
Viewing all articles
Browse latest Browse all 139

ደሀ ደንብ- የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም

$
0
0

ዳኝነት ሳይከፈል፣ በነፃ መዝገብ ማስከፈት

ክስ ለማቅረብ የፈለገ ወገን ከፍርዱ ለሚያገኘው የዳኝነት አገልግሎት መክፈል የሚገባውን የዳኝነት ገንዘብ ለመክፈል የሚያስችል የገንዘብ አቅም የሌለው ከሆነ ክሱን ያለዳኝነት ገንዘብ በደሀ ደንብ መሠረት የማቅረብ መብት እንዳለው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 215 ተደንግጓል፡፡ ክሱን የሚያቀርበው ወገን ድሀ በመሆኑ ምክንያት የዳኝነት ገንዘብ ሳይከፍል ክሱን አቅርቦ እንዲያሰማ ሊፈቅድለት ይገባል? የሚለው ጉዳይ ሊለይ የሚችልበት ዝርዝር አፈፃፀም ደንቡም ፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 467 እና ተከታዩ ድንጋጌዎች ተመልክቷል፡፡

እነዚህ ደንቦች ተፈፃሚነታቸው ክስ ለማቅረብ በፈለገ የተፈጥሮ ሰውም ሆነ በሕግ ሰውነት ያላቸው ወገኖችም ጭምር ነው፡፡

በዚህም መሠረት ድሀ ነኝ፤ መብቴን ለማስከበር ያለኝ ፍላጐቴ በዳኝነት ገንዘብ እንቅፋት ምክንያት ሊሰናከል አይገባም፡፡ ስለሆነም በድሀ ደንብ መሠረት ክሱን በነፃ እንዳሰማ ይፈቀድልኝ የሚል ማናቸውም ከሳሽ ድሀ መሆኑን ሊያመለክት የሚችል የሚገኝበትን የገንዘብ አቋም ማረጋገጥ ይገባዋል፡፡ ይህም ከሳሹ የሚገኝበት የገንዘብ አቋም ከተረጋገጠ በኋላ ለክሱ ሊከፈል የሚገባው የዳኝነት ገንዘብ መጠን ከሳሹ ከሚገኝበት የገንዘብ አቋም አኳያ ተገናዝቦ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 467 መሠረት ድሀ የመሆኑና ያለመሆኑ ጉዳይ ሊለይ ይገባል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 79555 ቅጽ 14፣[1] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 215፣ 467

አንድ ሰው በፍርድ ሊያልቅ የሚገባው ጉዳይን ፍርድ ቤት ይዞ ሲቀርብ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ መክፈል ያለበት መሆኑን የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 215፣ ከ467 እስከ 479 ድረስ የተደነገጉት ድንጋጌዎች ያሳያሉ፡፡ የዳኝነት አገልግሎት መክፈል የማይችል ሰው ክስ ለማቅረብ የሚችልበት አግባብ ስለመኖሩም ተጠቃሽ ድንጋጌዎች ያስገነዝባሉ፡፡ አንድ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ለመክፈል የማይችል ሰው በደሃ ደንብ ክስ ለማቅረብ የሚችል ሲሆን ለመክፈል አቅም እያለው ክስ ያቀረበ መሆኑ ከተረጋገጠ ግን መዝገቡ እንደሚዘጋ፣ የተዘጋ መዝገብ ደግሞ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ /ገንዘቡን/ ለመክፈል ዝግጁ እስከሆነ ድረስ የሚንቀሳቀስለት መሆኑን የሥነ ሥርዓት ሕጉ ድንጋጌዎች መንፈስና ይዘት ያስገነዝባሉ፡፡

ሰ/መ/ቁ. 52942 ቅጽ 12፣[2]  ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 215፣ 467-479

ይግባኝ

ዳኝነት ሳይከፈል በነፃ ለመክሰስ እንዲፈቀድ በቀረበ ጥያቄ ላይ ሊሰጥ የሚችለው ትእዛዝ እንደነገሩ ሁኔታ ሁለት ዓይነት ነው፡፡ አንደኛው ከሣሽ የዳኝነት ገንዘብ ለመክፈል የሚያስችለው የገንዘብ አቅም የሌለው ስለሆነ እንደ ጥያቄው የዳኝነት ገንዘብ ሳይከፍል በነፃ ፋይል ከፍቶ ክሱን ለማቅረብ ይችላል የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከሣሹ ድሃ ያለመሆኑ ስለተረጋገጠ ተገቢውን የዳኝነት ገንዘብ ካልከፈለ በቀር በነፃ ፋይል ከፍቶ ክሱን ለማቅረብ አይችልም የሚለው ነው፡፡

በመጀመሪያው አኳኋን ትእዛዝ በተሰጠ ጊዜ በዚህ ትእዛዝ መሠረት ፋይሉ ተከፍቶ ክርክሩ የሚቀጥል ነው፡፡ የክርክሩ ውጤት የሚታወቀው ግራ ቀኙ በሚያቀርቡት የፍሬ ነገርና የሕግ ክርክር ማስረጃ መሠረት ነው፡፡ በመጨረሻው የክርክር ውጤት ተከሣሹ ባይስማማ ክርክሩ ከመጀመሩ በፊት ክሱ ዳኝነት ሳይከፈልበት በነፃ እንዲከፈት መደረጉ የሕግ ድጋፍ አልነበረውም የሚለውን እንደ አንድ የይግባኝ ምክንያት በማድረግ በውሣኔው ላይ ካለው ቅሬታ ጋር አዳምሮ ማቅረብ ይኖርበታል እንጂ ከሥረ-ነገሩ ፍርድ በፊት የይግባኝ አቤቱታ የማቅረብ መብት አይኖረውም፡፡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 320/3/ የተመለከተው ድንጋጌም በዚህ አኳኋን በሚቀርበው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ክልከላ ለማድረግ ነው፡፡

በሌላ በኩል “ድሀ ያለመሆንህ ተረጋግጧል፡፡ የዳኝነት ገንዘብ ካልከፈልክ በቀር ፋይል አይከፈትም” ለተባለው ከሣሽ ግን ይህ ዓይነቱ ትእዛዝ የመጨረሻ ነው፡፡ ሌላ የሚጠበቅ የሥረ-ነገር ፍርድ የለውም፡፡ ስለሆነም የዳኝት ገንዘብ ለመክፈል አቅም ሳይኖረኝ ክርክሬና ማስረጃዬ በአግባቡ ሳይታይ አቅም እንዳለኝ ተቆጥሮ የዳኝነት ገንዘብ ክፈል መባሌ ተገቢ አይደለም የሚል ከሆነ የተሰጠው ትእዛዝ የመጨረሻ እንደመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 320/1/ መሠረት የይግባኝ አቤትታ የማቅረብ መብት አለው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 23744 ቅጽ 6፣[3] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 320

[1] አመልካች ቤተልሄም ፋርማሲ ቲዩካል ኃ/የተ/የግል/ማህበር ተጠሪ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ታህሳስ 02 ቀን 2005 ዓ.ም.

[2] አመልካች አቶ ገብሩ ኮሬ እና ተጠሪ አቶ አመዲዮ ፌዴሬቺ ጥቅምት 18 ቀን 2003 ዓ.ም.

[3] አመልካች አቶ በቀለ በድዬ እና መልስ ሰጪ እነ የወጋገን ባንክ አዋሳ ቅርንጫፍ /3 ሰዎች/ ሐምሌ 26 ቀን 1999 ዓ.ም.


Filed under: Articles, Case Comment

Viewing all articles
Browse latest Browse all 139

Trending Articles